ለሠላማችን ዘብ እንቁም

የሰላም መጥፋት በሴቶች ላይ የሚያደርሰው ተጸኖ ፤
• የጠላትን ልጅ ወልዶ ማሳደግ መባርክ ወይስ መረገም?
ሴቶች በአለማችን ውስጥ በሚደረጉት ግጭቶችና ጦርነቶች ሁሉ እንደማንኛውም ሰው፤ የግጭቱ ሰለባዎች ይሆናሉ ። ይፈናቀላሉ፤ ይሰደዳሉ፤ ይራባሉ፤ ይጠማሉ። ሆኖም ችግራቸው በዚህ ብቻ አያበቃም። ሴቶች በተጨማሪ በሴትነታቸው ብቻ እጅግ አሰቃቂ የሆኑ ተደራራቢ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። በግጭቱ ምክንያትባላቸውን፣ ልጆቻቸውን፣ ሃብትና ንብረታቸውን፤ ባጠቃላይ ህልውናቸውንና ሰላማቸውን ያጣሉ። ይህ ሁሉ ግፍ አልበቃ ብሎ የባሎቻቸውና የልጆቻቸው ገዳዮች በሆኑ ወንዶች ይደፈራሉ። በዚህ ዓይነት ከባሎቻቸውና ከልጆቻቸው ገዳዮች ይፀንሳሉ (ያረግዛሉ)። መቼም አንዴ ከተረገዘ መወለዱ አይቀርምና ይወልዳሉ። ይህን አምርረው ከሚጠሉት ጠላታቸው የወለዱትን ልጅ ምን ያድርጉት??? አቅፈው እንዳይስሙት የጠላታቸው ማለትም የባላቸውና፣ የልጆቻቸው ገዳይ ልጅ ነው። እንዳይተዉት ዘጠኝ ወር አርግዘው ተጨንቀው አምጠው የወለዱት ልጅ ነው። “ላም እሳት ወለደች እንዳትልሰው እሳት፤ እንዳትተወው ልጅ ሆነባት” እንደሚባለው።
ኢሰብአዊ በሆነ መንገድ የወለደችውን እናት እንተዋትና የተወለደውን ልጅ ደግሞ እናስበው። በተለይ ይህ ልጅ ከአንድ ነፍሰ ገዳይ ሰው የተወለደ መሆኑን የሚያውቁ ሁሉ ቤተስብም፤ ጎረቤቱም እንዴት ያዩታል፤ ይቀበሉታል? ይህ ህጻን ወላጆቹን መርጦ አልተወለደም። ሆኖም በግጭቱ ምክንያት ቤተሰባቸውን፣ ሃብት ንብረታቸውን ያጡ ህጻኑን ባዩ ቁጥር ምን ትዝ ይላቸዋል? ይህ ልጅ ከጨካኝ አባት ስለተወለደ፤ በዘመኑ ሁሉ እየተጠላና እየተረገመ ሲያድግ የሚደርስበትን የስነልቦና ጭንቀትና ህመም መገመት አያዳግትም ። እናትም ብትሆን ስትናደድ “ክፉ ያባቱ ልጅ“ ትለው ይሆን? ይህ ሁሉ መከራ የሰላም መጥፋት ወጤት ነው።
ስደትና መፈናቀል የሰላም መጥፋት በተለይ በሴቶች ላይ የሚያደርሰው ጫና እጅግ ብዙ ነው ብለናል ።
ስደትና መፈናቃል ድንገት የሚያጋጠሙ ወይም የሚከሰቱ ችግሮች ስለሆኑ በተለይ እርጉዝ ለሆኑና ህጻናትን ይዘው ለሚፈናቀሉ ወይም ለሚሰደዱ እናቶች እጀግ ከባድ ነው። አሁን በቅርብ ጊዜ እንኳን በሃገራችን በተደጋጋሚ በደረሱ ስደቶችና መፈናቀሎች፤በየመንገዱና በየተጠለሉባቸው አጸደ አብያተክርስቲያናት ግቢ ውስጥም የወለዱ እህቶቻችን እነደነበሩ ስምተናል። ምጥ ቦታ አይመርጥም፣ ሁኔታዎች እስኪመቻቹም አይጠብቅም ከማንም ቁጥጥር ውጪ በጊዚው የሚሆን ነገር ነው። ምናልባት የህክምናው ነገር እንደ ቅንጦት እንኳን ቢታይ፤ ከዚያ ያነሰ ነገር ባልተሟላበት ሁኔታ አንዳንድ እህቶቻችን ውሃ በሌለበት ልጅ እነደወለዱ ስምተናል። ሴት ልጅ ውሃ በሌለብት ልጅ ወልዳ የሚደርስባትን የአእምሮ ጭንቀት በተለይ ልጅ የወለድን ሴቶች እንደምንረዳው ጥርጥር የለኝም። በዚያ ዓይነት ሁኔታ እናትና ልጅ ውሃ ሳይጠጡና ሳይታጠቡ ስንት ቀን ይቆዩ ይሆን?
ሴቶች እህቶቼ እስቲ አስቡት ምንድነው የሚደርገው? ይህ እውነትና እየሆነ ያለ ሃቅ ነው። ሌላው ቢቀር ወላድና ወሃ ተለያይተው እንዴት ይዘለቃሉ? እንስሳት እንኳን ተፈጥሯቸው ስለሆነ የወለዱትን ግልገል ወይም ልጅ በምላሳቸው ልሰው ያጸዱታል እስቲ አስቡት የሰላም መጥፋት በሴቶች እህቶቻችን ላይ የሚያደርስውን መከራ!!! ምን እናድርግ? እኔ በተለይ “ውሃ በሌለበት ልጅ መውለድ” ቀላል የሚመስል ግን እጅግ ከባድ ልብ የሚሰብር ነገር ሆነብኝ። ስለዚህ ስለ ሰላም ዝም አንበል። ሰላም ለእያንዳንዳችን፤ ለአገራችን፤ ለወገኖቻችን አስፈላጊ ስለሆነ ስለ ሰላም እንጸልይ !! እናስተምር!! ስለሰላም እንምከር!! ከራሳችን ቤት እንጀምር። ሰላምን የሚያናጋ መልእክት በማኅበራዊ መድረክ ማስተላለፍ፤ ማሰራጨት እናቁም፤ ስለፍቅር እናውራ።
ሁላችንም ለሰላም ዘብ እንቁም!!

በትርሲት ሽበሺ
If you have any question, please contact the author tersite1@gmail.com